በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት እና አለመረጋጋት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲገኝለት የቀረበ ጥሪ

 

እኛ ሥማችን ከዚህ መግለጫ ግርጌ የተዘረዘረው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአማራ ክልል የተከሰተው
ግጭት እጅግ አሳስቦናል። ግጭቱን ለመቆጣጠር እና ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ክልሉ “በመደበኛ የሕግ
ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች” ሆኖብኛል በሚል ለፌዴራል መንግሥቱ አስፈላጊውን የሕግ ማዕቀፍ
እንዲተገብር መጠየቁን ሰምተናል። ይህንን ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተፈፃሚነቱ በክልሉ እና
እንዳስፈላጊነቱ በሌሎችም አካባቢዎች የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሐምሌ 28 ጀምሮ ማወጁን አሳውቋል።
ግጭቶችን የመከላከልና ሰላም የማስፈን ጉዳይ ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን እናምናለን።
ይሁንና ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥር እየሰደዱና እየተስፋፉ ከመሆኑ አንፃር፣ ግጭቶችን ለማስቆም
የሚወሰዱ እርምጃዎች የብዙኃንን ደኅንነት፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች አደጋ ላይ የማይጥሉ
እንዲሆኑ፤ እንዲሁም የግጭቱ መነሻ መንስዔዎች በሚመለከታቸው አካላት ተለይተው የሚቀርቡ ዘላቂ
የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ሁሉን አካታች ምክክሮች እንዲካሔዱና በአግባቡም መተግበር እንዳለባቸውም
እንረዳለን።
ስለሆነም፣ የሚመለከታቸው አካላት፣
● ግጭቶች በሰላማዊ ዘዴዎች የሚፈቱባቸውን መንገዶች ለማግኘት የሲቪል ማኅበራት፥ የፖለቲካ
ፓርቲዎች፥ የእምነት ተቋማት፣ መገናኛ ብዙኃን፣ እና የአገር ሽማግሌዎች የተከሰተው ግጭት
በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የበኩላቸውን ግፊት እንዲያደርጉ፤ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች
የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች እና ሥምምነቶች በአማራ ክልልም በሚንቀሳቀሱ ወገኖች እና በፌዴራሉ
እና የክልሉ መንግሥታት መካከል መደረግ የሚችልበት ዕድል እንዲፈለግ፣
● ትጥቅን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች በሰብዓዊ መብቶች እና በሰብዓዊ ሕግጋት (humanitarian laws)
እንዲመሩ እና የንፁኃን ደኅንነት እንዲጠበቅ፤ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች
የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ እና ሌሎችም ጉዳቶች
በክልሉ እንዳይፈፀሙ ከፍተኛ የመከላከል ሥራዎች እንዲከናወኑና የተጠያቂነት ስርዓት እንዲዘረጋ፣
● በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም ወቅት የፀጥታ አካላት ያልተመጣጠነ ኃይል እንዳይጠቀሙ፣
ብሔርን መሠረት ያደረጉ ማግለሎች እና ጥቃቶች እንዳይስፋፉ እና የጅምላ እስሮች
(Indiscriminate mass arrests) እንዳይከናወኑ፣
● የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እና ብዙኃን መገናኛዎች ግጭት አገናዛቢ አዘጋገብን
እንዲተገብሩ፣ የሐሰተኛ እና የተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት እንዲገቱ፣ እንዲሁም ሐቁን የሚያንፀባርቁ
መረጃዎችን ብቻ ለዜጎች በማድረስ ከግጭት አባባሽነት እንዲቆጠቡ፣
● የዜጎች የመገናኛ ዘዴዎች እና ሌሎችም መሠረታዊ አገልግሎች እንዳይቋረጡ ማድረግ እና ሰብዓዊ
እርዳታዎች ለሚያስፈልጓቸው በተለይም በአማራ ክልልና አጎራባች አካባቢዎች በሚገኙ የአገር
ውስጥ ተፈናቃዮች ባሉባቸው ቦታዎች በአግባቡ እንዲደርሱ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ፣
● ዝርዝር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ለማስፈጸም የሚወጡ መመሪያዎችና ደንቦች ለዜጎች ተዳራሽ በሆኑ
አማራጮች በተከታታይ እንድደርሱ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ሰላም ለኢትዮጵያ!
ይህንን የሰላምና የዘላቂ መፍትሔ ጥሪ ያቀረብን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚከተሉት ነን።
1. የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)
2. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል
3. የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር
4. የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት
5. አዲስ ፓወርሀውስ
6. የኢትዮጵያ ሴቶችና ሕፃናት ማኅበራት ኅብረት
7. የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች
8. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት
9. ሴታዊት ንቅናቄ

Related posts