አላግባብ የታሰሩ የኢሰመጉ ሠራተኞች በአስቸኳይ ይፈቱ!

ጋዜጣዊ መግለጫ

                                                                                         አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 28 ቀን 2015 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በቀን ታኅሣሥ 27፣ 2015 ባወጣው መግለጫ እንዳሳወቀው፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ አለም ገና አካባቢ እየተካሔደ ባለው ቤት የማፍረስ ዘመቻ ምክንያት ቤታቸው የፈረሰባቸው ግለቦች ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ጉዳዩን የሚያጣሩ ባለሙያዎችን ወደ ቦታው ልኮ ነበር። በቦታው በመገኘት ጉዳዩን እንዲያጣሩ የተመደቡት 3 ባለሙያዎች እና የድርጅቱ ሾፌር እንዲሁም የድርጅቱ መኪና በፖሊስ ተይዘው አለም ገና አካባቢ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ኢሰመጉ ገልጿል። ኢሰመጉ በተጨማሪም ከሚሠራው ሥራ ጋር በተገናኘ ጫና እና ማስፈራራት እየደረሰበት እንደሚገኝ አስታውቋል።
ይህ ድርጊት ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዓላማ እንዳይፈፅም እና ሠራተኞቹም የሙያ ነጻነታቸውን ጠብቀው
እንዳይሠሩ የሚያደርግ ተግባር ከመሆኑም በተጨማሪ የሲቪክ ምኅዳሩን የሚያጠብ እና የሲቪል ማኅበረሰብ
ድርጅቶች ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የሚሠሩትን ሥራ የሚያደናቅፍ፣ በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ላይ
የሚሠሩ ሌሎች ተቋማትንም የሚያሸማቅቅ ድርጊት ነው።
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ኅብረትን ዓለም ዐቀፍ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ
መብቶች ሰነዶችን አፅድቃለች። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ከአንቀፅ 29 እስከ 31 የመናገር ነፃነትን፣
የመሰብሰብ ነፃነትን እና የመደራጅት እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን በግልፅ አስቀምጧል። በቅርቡ
የተከለሰው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 በኢትዮጵያ ለመብቶች የመሟገት ሥራ
ለሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ቢሆንም፥ ከዚህ በፊት ከተስተዋሉ ቀጥተኛ
እና ተዘዋዋሪ ጫናዎች በተጨማሪ የኢሰመጉ ባለሙያዎች እስር የሲቪክ ምኅዳሩ ላይ የማይገባ አሻራ
እያሳረፉ ነው።
ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም ዐቀፋዊና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብቶች ሥምምነቶችን እንዲ በሕገ
መንግሥቱ ጥበቃ የተደረገላቸውን ሰብዓዊ መብቶች የማክበር፣ የማስከበር እና ሰብዓዊ መብቶች
የሚከሩበትን ሁኔታ የማሟላት ኃላፊነት አለበት።
ስለሆነም፣ እኛ ሥማችን ከዚህ መግለጫ ግርጌ የተዘረዘርን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የታሰሩት
የኢሰመጉ ሠራተኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንዲሁም የዘፈቀደ እስራቱን የፈፀሙት የመንግሥት አካላት
በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ አበክረን እንጠይቃለን።
የጋዜጣዊ መግለጫው ፈራሚ ድርጅቶች ዝርዝር
1. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት (ኢሰመድህ)
2. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)
3. የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)
4. የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች (LHR)
5. የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ሴቶች ማኅበር (EWLA)
6. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC)
7. የኢትዮጵያ ሴቶችና ህጻናት ማኅበራት ኅብረት (UEWCA)
8. ሴታዊት ንቀናቄ (Setaweet)
9. ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ (IAG)
10. ስብሰብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (AHRE)
11. የሴቶች ህብረት ለሰላምና ለማህበራዊ ፍትህ (WASP)
12. የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት (NEWA)

Related posts