የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች የሚገለጹት በሚሠሩት ስራ እንጂ በማንነታቸው አይደለም፡፡
“የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች” ተብለው የሚገለፁት በግል ማንነታቸው፣ ባህሪ ወይም የማንነታቸው መገለጫ በሆኑ የወል መጠሪያዎች ሳይሆን በሰላማዊ መንገዶች ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበርና ለማስጠበቅ በሚያደርጓቸው ጉልህ ተግባራት ወይም ስራዎች ብቻ የተመሰረተ ነው። በዚህም የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች፡-እንደ ጋዜጠኛ፣ ጠበቃ፣ ፖሊስ፣ የማህበረሰብ አንቂ፣ የሰብአዊ ድጋፍ ወይም መብት ባለሙያ፣ የሕክምና ባለሙያ እና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ የማህበረሰቡ አባላት ወይም ማንኛውም ለሰብአዊ መብቶች መከበር አስተዋፅኦ የሚያደረጉ ግለሰቦች፤ እንዲሁም እንደ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ወይም የሰራተኛ ማህበር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ቀደም ሲል በሰብአዊ መብት ሥራዎች ሲሳተፉ ቆይተው በሂደት ግን ወደ አመጽ እና የመብት ጥሰቶችን በሚያስከትሉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎ ወደ ማድረግ ከተሸጋገሩ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾችነታቸውን እንደተውት ይቆጠራል፡፡ ለሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች የሚደረጉ ጥበቃዎችንም ሆነ ማናቸውንም አይነት ድጋፎችን ያጣሉ። የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ሰብአዊ ክብርን ለማስጠበቅ እና የሰዎችን መብት ለማስከበር ከግል ጥቅማቸው ባለፈ ለሌሎች ሰዎች መብቶችና ነጻነቶች መከበር የሚሰሩ ሰዎች በመሆናቸው የሞራል ልህቀት ማሳያዎች ሊባሉ ይችላሉ፡፡
ሁሉም የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ከሁከት እና ግጭት እንዲርቁ፣ መብቶችን ከመጣስ እንዲቆጠቡ እና የስነ-ምግባር፣ የሞራል እና የህሊና ምሳሌ እንዲሆኑ ማዕከላችን አበክሮ ይጠይቃል።