የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 19/2017 በ6ኛው ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ባካሄደው 2ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013ን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር እይታ ለዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል። እኛ ሥማችን ከዚህ መግለጫ ግርጌ የተዘረዘረው ከጋዜጠኞች የሙያ ማህበር እና የሰብዓዊ መብት ድርጅቾች የአዋጁ ማሻሻያ አስፈላጊነት ላይ ገለልተኛ ጥናት ባልተደረገበት፣ በቂ የባለድርሻ አካላት ውይይትም ባልተካሔደበት ሁኔታ ረቂቁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ መቅረቡ፣ እንዲሁም በአዋጁ ከለላ ተሰጥቷቸው የነበሩ የቁጥጥርና ሚዛን መጠበቂያዎች በረቂቅ አዋጁ ሊሻሩ የሚችሉ መሆናቸው በእጅጉ ስላሳሰበን ይህንን የአቋም መግለጫ አዘጋጅተናል።
እንደሚታወቀው በአገራችን በ2010 ከተካሄደው የፖለቲካ ለውጥ ጋር ተያይዞ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት ያስችላሉ የተባሉ በርካታ የሕግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። በዚህ ረገድ ከተወሰዱት ዕርምጃዎች አንዱ በሚዲያ ዘርፉ የተወሰደው ማሻሻያ ሲሆን፣ ይህም አዲስ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ሆኖ እንዲፀድቅ አስችሏል። የዚህ አዋጅ መጽደቅ በአገራችን ነጻና ገለልተኛ የሚዲያ ምኅዳር ለመገንባት ከፍተኛ ተስፋ አሳድሮ ነበር። የአዋጁ ይዘትም ከዓለም ዐቀፍ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች ጋር የተጣጣመ እና ለፕሬስ ነጻነትና የተሻለ የሚዲያ ሥራ መሠረት በመሆኑ አዋጁ በስፋት ተቀባይነትን አግኝቶ ቆይቷል። ምንም እንኳን ተለዋዋጭ በሆነው የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያት የሚዲያ ነፃነትን ከማረጋገጥ አንጻር የሕጉ ተፈጻሚነት በተግባር ችግሮች እየገጠሙት ቢሆንም ይህ አዋጅ እስካሁን የገለልተኛ ጋዜጠኝነትና የመገናኛ ብዙኃን መብቶች ጥበቃ ዋነኛው መለኪያ ይሆናል ተብሎ ይታመናል። አዋጁ በሚዲያ ምኅዳሩ ላይ የሚኖረው አዎንታዊ አስተዋፅዖም ረዘም ያለ ጊዜ እና ትዕግስት የሚጠይቅ መሆኑም ይታወቃል።
ይሁን እንጂ አሁን በአስፈፃሚው አካል ተረቅቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ የቀረበው ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ በሥራ ላይ የሚገኘውን የመገናኛ ብዙኃን ሕግ በርካታ አንቀፆች ይዘትና መንፈስ የሚቀይር መሆኑን ተገንዝበናል። ረቂቅ ማሻሻያው የአካሄድና የይዘት ግድፈቶች በስፋት የሚስተዋሉበት ሲሆን፣ በረቂቁ ማሻሻያ ላይ ምንም ዓይነት የሕዝብ ውይይቶች ባለመከናወናቸው የሲቪል ማኅበረሰቡን፣ የሚዲያ ሙያተኞችን እንዲሁም የሌሎች መብቶች ተሟጋቾችንና የማኅበረሰብ ድምፆች እንዳይሰሙ አድርጓል። ማሻሻያውን ለማዘጋጀት የተሔደበት መንገድ ግልጽነትና አሳታፊነት የጎደለው ሲሆን፣ የረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት በገለልተኛ አካል በተሠራ ጥናት ስለመለየቱ የቀረበ ማስረጃ የለም።
በሌላ በኩል የረቂቅ አዋጁ የተለያዩ አንቀፆች በሥራ ላይ የሚገኘው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ጥበቃ የሚሰጣችውን ነጻነቶች የሚገድብና የሚዲያ ተቆጣጣሪውን አካል በአስፈፃሚው አካል ተፅዕኖ ውስጥ ይከተዋል የሚል ስጋት አለን። ለምሳሌ ያህል የነባሩን አዋጅ አንቀጽ 8 (2) ዋና ዳይሬክተሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለሚሾምበት የሚደነግገው ክፍል፤ አንቀጽ 9 (1 እና 2) የቦርዱ አባላት እጩዎች የሚመለመሉበትና የሚፀድቁበት ሒደት ለሕዝብ ግልጽ መሆን እንዳለበት የሚደነግገው ከፍል፤ አንቀጽ 11 (6) የቦርዱ አባላት ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ወይም ተቀጣሪነት የሚከለከሉበትን ሁኔታ የሚደነግገው ክፍል መሰረዝ ዋና ዋና የይዘት ለውጦች ናቸው፡፡ በተያያዘም በአዲሱ ማሻሻያ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሹመት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሰጠቱ፤ እንዲሁም በነባሩ አዋጅ ለቦርዱ ተሰጥተው የነበሩት የፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት አለማደስ፣ ማገድ፣ መሰረዝ፣ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት የመሳሰሉት ኃላፊነቶች አሁን ለባለሥልጣኑ መሰጠታቸው ሥልጣንን ጠቅልሎ ለአንድ አካል ከመስጠትና በሒደትም ላልተገባ ተፅዕኖ በር ከመክፈቱ በተጨማሪ ከላይ የተጠቀሱት የማሻሻያው አንቀፆች በአንድነት ሲነበቡ የነባሩን አዋጅ አንቀጽ 7 (የባለሥልጣኑን ገለልተኝነትና ነፃነት) ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ረቂቅ አዋጅ ያደርገዋል።
በተያያዘም ረቂቅ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚቀርብበት ወቅት ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምክር ቤት አባላት ጭምር ተቃውሞ ገጥሞት የነበረ ቢሆንም በቂ የባለድርሻ አካላት ውይይት ሳይደረግበት ወደቋሚ ኮሚቴ መመራቱ በጉዳዩ ላይ የሕዝብን ድምፅ በተገቢ ላለማካተቱ ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
በመሆኑም እኛ በሰብዓዊ መብቶችና ሚዲያ ነጻነት ላይ የምንሠራ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ከረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ ሒደት ጋር በተያያዘ በርካታ ጉዳዮች እንደሚያሳስቡንና አስችኳይ መፍትሔም ሊፈለግላቸው እንደሚገባ በአጽንኦት ለማስገንዘብ እንወዳለን። ይህንን መግለጫ ያወጣነው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር፤
- የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት ላይ በጥናት የተደገፈ ማስረጃ እንዲቀርብ እና በባለድርሻ ወገኖች ሰፊ ውይይትና መግባባት እንዲደረስበት፣
- በጥናቱ እና ውይይቱ መሠረት ማሻሻያ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑ ከታመነበት፣
2.1.) የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በምክር ቤቱ ከመፅደቁ በፊት ትርጉም ያለውና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ውይይት እንዲከናወን፣
2.2.) የውይይቶቹ ግብዓቶች በአግባቡ ተካትትው ረቂቁ እንዲዳብር፣ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ መንፈስ ዴሞክራሲን ከማስፈንና የመገናኛ ብዙኃንን ነጻነትን ከማረጋገጥ አንፃር የነበረውን አስቻይ የሕግ ማዕቀፍ የሚንድና ወደኋላ የሚጎትት እንዳይሆን በአጽንኦት እንጠይቃለን።
በመጨረሻም የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ የመገናኛ ብዙኃንን ነፃነት እና ሐሳብን የመግለጽ መብት ጥበቃን በሚያጠናክር መልኩ እንዲስተካከል የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።
የዚህ መግለጫ ፈራሚ ድርጅቶች፣
- የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD)
- የህግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች (LHR)
- የኢትዮጵያ ሰራተኞች መብቶች ተሟጋች (ELRW)
- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (EHRCO)
- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC)
- የኢትዮጵያ ሴቶች ድርጅቶች ጥምረት (NEWA)
- የኢትዮጵያ ሴቶች መብቶች ተሟጋች (EWRA)
- የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር (EWLA)
- ሴታዊት (Setaweet)
- ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (AHRE)
- የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር (EMMPA)
- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት (CEHRO)
- የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር (EMWA)
- ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ (HRFE)