የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በጋዜጠኞቹ መፈታት የተሰማውን ደስታ ይገልጻል

April 7, 2022

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በህጋዊ መንገድ በመዝገብ ቁ. 5220 እና አዋጅ ቁ.1113/2019 የተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ ማዕከሉ ሁሉንም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞችን ለመጠበቅ እና ለመከላከል የሚሰራና ጠንካራ ሀገራዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ስብስብን ለመፍጠር እየሰራ ያለ ሀገር በቀል ተቋም ነው። ማዕከሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችንና ጋዜጠኞችን አቅም ለማሳደግ እና መብቶቻቸው እንድከበሩላቸው ይሰራል። 

እንደሚታወቀው ጋዜጠኞች መረጃን በማቅረብ ዜጎችን ለማንቃት እና በሀገራቸው ጉዳይ ላይ መረጃን የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። በአለም አቀፍ ደረጃ ለጋዜጠኞች ጥበቃ ለማድረግ የወጡ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች መሰረት ጋዜጠኞች ደህንነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆንና መብቶቻቸው እንዲጠበቁ፤ በተለይም መረጃ የማግኘት እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶቻቸው ከለላ እንዲደረግላቸው ይደነግጋሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ከቀርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ በጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ ያለው የዘፈቀደ እስር በእጅጉ እንደሚያሳስበው በተለያዩ ጊዜያት በሚያወጣቸው መግለጫዎች ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡  

ማዕከላችን ጋዜጠኛ አሚር አማን እና ከሥራ ባልደረባው የካሜራ ባለሙያ ቶማስ እንግዳ ጋር በዋስትና በመፈታታቸው የተሰማዉን ደስታ ይገልጻል፡፡ ሁለቱም ከኅዳር 19 ቀን 2014 ዓ/ም ጀምሮ ለ120 ቀናት በእስር ከቆዩ ብኃላ መጋቢት 20/2014 ዓ/ም በ60 ሺ ብር ዋስትና ተፈተዋል፡፡ ጋዜጠኞቹ ለዚሁ ሁሉ ቀናተ ያለምንም ክስ መታሰራቸው አግባብ ባይሆንም በዋስትና ተፈተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀል መቻላቸው ማዕከላችን በአውንታዊ ጎኑ ይመለከተዋል። 

በተመሳሳይ ሁኔታም የተራራ ኔትወርክ መስራችና ዋና አዘጋጅ የሆኑት ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከመኖሪያ ቤታቸው በፖሊስ ተይዘው ከታሰሩ ከ117 ቀናት በኋላ መጋቢት 27/2014 ዓ/ም በ50 ሺ ብር ዋስ እንዲለቀቁ በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተወሰነው መሰረት መጋቢት 28/2014 ከእስር ተለቀዋል፡፡ ማእከላችን በጋዜጠኛ ታምራት ነገራ መፈታት የተሰማውን ደስታ እየገለጸ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በጋዜጠኞች እና በሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ላይ የሚያደርሰውን ተመሳሳይ ህገ-ወጥ እስር እና እንግልት በዘለቄታው እንዲያቆም እና ለጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ እናሳሰባለን፡፡ የመብት ጥሰት የፈጸሙ የመንግስት አካላትንም ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሕጋዊ ሥርዓት እንዲያስፍን እንጠይቃለን፡፡ 

 

 

 

Related posts