የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ
ጳጉሜ 1 ቀን 2015
በመገባደድ ላይ የሚገኘው 2015 ለአገራችን ኢትዮጵያ ሁለት ገጽታዎች አሉት፤ በአንድ በኩል የሰላም ጅምር ተስፋ ይዞ ቢመጣም፥ በሌላ በኩል ደግሞ ግጭቶች ተባብሰው በዜጎች ሕይወትና የአገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን የዚህ የሰላም እጦት ዳፋም ለመጪው አዲስ ዓመት ሊያወርስ ዋዜማው ላይ እንገኛለን።
እኛ ሥማችን ከዚህ የሰላም ጥሪ ግርጌ የተዘረዘረው አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከአገራችን ወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ በሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብቶች ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ከመሥራት ባሻገር፣ በተናጠልም ይሁን በጋራ የተለያዩ ይዘት ያላቸውን መግለጫዎች እና ጥሪዎች ስናደርግ መቆየታችን የሚታወስ ነው። ከነዚህም ጥሪዎች መካከል አምና እና ካቻምና በአዲስ ዓመት ዋዜማ ያወጣናቸው የሰላም ጥሪዎች የሚታወሱ ናቸው። መጪው አዲስ ዓመት መንግሥት ሁሉን ዐቀፍ የሰላም መድረክ በመፍጠርና ግጭቶችን በመከላከል፣ የሰላም እጦቱ በዘላቂነት የሚፈታበት የአጭር፣ የመካከለኛ፣ እና የረዥም ጊዜ መፍትሔዎች የሚቀየሱበት እንዲሆን ጥሪያችንን እንደሚከተለው እናቀርባለን።
ያሳለፍነው ዓመት መባቻ የትግራይ ክልል ጦርነት የተፋፋመበት የነበረ ቢሆንም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተደረገው የፕሪቶሪያ የሰላም ንግግር ለሁለት ዓመታት የዘለቀው እና ብዙ ሰብዓዊ እልቂት እና ቁሳዊ ውድመት ያስከተለው ግጭት ከጥቅምት 23፣ 2015 ጀምሮ በሰላማዊ መፍትሔ እንዲጀመር አስችሏል። ይህም ፈቃደኝነቱ ካለ የትኛውንም ዓይነት ግጭት በሰላም ለመፍታት እንደሚቻል ትምህርት ሰጥቷል ብለን እናምናለን። ይሁንና ዘንድሮም እልባት ያልተገኘላቸው ግጭቶች በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ያሉ ሲሆን፥ በዚሁ ዓመት የተስተዋሉ አዳዲስ እና ነባር ግጭቶች በመጪው ዓመትም ተባብሰው እንዳይቀጥሉ ያሰጋል።
በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ጋር የቀጠለው ውጊያ፣ በአማራ ክልል ከየልዩ ኃይሉን መፍረስ ጋር ተከትሎ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር የተቀሰቀሰው እና ተባብሶ የቀጠለው ግጭት፣ እስከ አሁንም ድረስ ምርጫ ማካሔድ ያልተቻለበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ያለው አለመረጋጋት፣ በጋምቤላ ክልል ተደጋግሞ የሚስተዋለው የእርስ በርስ ግጭትና አለመረጋጋት፣ ከደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መልሶ መዋቀር ጋር የተያያዙ ሕዝባዊ ቅራኔዎች እና ተቃውሞዎች፣ በኦሮሚያ ክልል የተካሄዱ አስተዳደራዊ መዋቅር ለውጦች ያስከተሉት ግጭት፣ መፈናቀል፣ ቅራኔና ተቃውሞዎች፣ በቤተ እምነቶች እና የፖለቲካ መሪዎች የተከሰቱ ውጥረቶች፣ በዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ላይ የተጣሉ ገደቦች፣የጅምላና የዘፈቀደ እስሮች፣ የጋዜጠኞች እና የመብቶች ተሟጋቾች መዋከብና እስራት፣ የአስገድዶ መሰወር ድርጊቶች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ግድያ፣ ያለመከሰስ መብት ያላቸውነ የሕዝብ ተወካዮች ማሰር፣ በጥቅሉ የፖለቲካ ምኅዳሩን የሚያጠቡ ሁኔታዎች ያገባደድነው ዓመት ኹነቶች ጥቅል ገጽታዎች ናቸው።
እነዚህ ኩነቶች እንዳሉ ሆኖ በኦሮሚያ ክልል የቀጠለውን ግጭት ለማስቆም የተደረገው የዛንዚባሩ የሰላም ድርድር ጅምር ሙከራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ሀይሎች ጋር የተደረጉ አንዳንድ ሥምምነቶችም ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ነበሩ። ከነዚህ በተጨማሪ ፣ በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ በፖሊሲ አማራጮች ላይ ውይይቶች መካሔዳቸው እና ለሕዝባዊ አስተያየት መቅረቡ እንዲሁም ለአገራዊ ምክክር የተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳ ማሰባሰብ በሀረሪ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሲዳማ እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መጀመራቸው አዎንታዊ እርምጃዎች ናቸው። እነዚህ ጅምሮች ትኩረት አግኝተው ሰላማዊ መፍትሔዎች የበለጠ ተቀባይነት እንዲያገኙ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት እና ጠንካራ ሥራ ያስፈልጋል።
መጪው የ2016 ዓመት ከላይ የጠቀስናቸውን እና የዜጎችን መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች እና ነጻነቶች የሚያጣብቡ ግጭቶች የሚቀጥሉበት እንዳይሆን በማሰብ በግጭቶች ውስጥ ለሚሳተፉ አካላት እና ደጋፊዎቻቸው፣ ለመንግሥት ኃላፊዎች፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለሲቪክ ማኅበራት፣ ለመገናኛ ብዙኃን እና ጋዜጠኞች፣ ለምሁራን፣ ለተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣ ለእምነት ተቋማት መሪዎች እና ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪያችንን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡
1ኛ) አገር ዐቀፍ የሰላም መድረክ ይመቻች!
ብዙዎቹ ነውጥ አዘል ግጭቶች የተቀሰቀሱትም ይሁን የተባባሱት ውጥረቶችን በፖለቲካዊ ንግግር እና ምክክር ሳይሆን በኃይል የመፍታት የቆየ ባሕል በመኖሩ ነው ብለን እናምናለን። ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉንም የማኅበረሰብ አካላት የሚያሳትፍ አገር ዐቀፍ የሰላም መድረክ (የሰላም ኮንቬንሽን) ተመቻችቶ የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛ ጊዜ እና የረዥም ጊዜ ግጭትን የመከላከል፣ የመፍታት እና የሰላም ግንባታ ሥራዎች የሚጠናከሩበት አገራዊ ፍኖተ ካርታ እንዲዘጋጅ፤
2ኛ) ገለልተኛ ምርመራና ተጠያቂነት ይስፈን!
ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ (victim centered) የተጠያቂነት ስርዓት መስፈን በሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና በግጭቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ፍትሕ የሚሰጥ ከመሆኑም ባሻገር፥ የበቀል አዙሪትን ለመግታት እና ለፍትሕ ተቋማት ተዓማኒነትም ዋልታ ነው ብለን እናምናለን። ለነውጥ አዘል ግጭቶች መንስዔ የሆኑ፣ ሕዝባዊ እና ብሔራዊ ጥቅምን የሚጎዱ እና ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው ውሳኔዎችን ያሳለፉ፣ በነውጥ አዘል ግጭቶች ውስጥ በመሳተፍ ንፁኃንን ያጠቁ፣ የጥላቻ ንግግሮችን እና ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮችን በአደባባይ ያደረጉ እና ንፁኃንን ለጥቃት ያጋለጡ አካላት በነጻ እና ገለልተኛ የፍትሐዊ የምርመራ እና የዳኝነት ሒደት ተጠያቂ እንዲደረጉ፣ የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በሐቀኝነት እና ሕዝባዊ ተቀባይነት ባለው መንገድ ወደ ተግባር እንዲገባ፤ በሒደቱም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ዓለም ዐቀፍ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች እንዲሳተፉ፤
3ኛ) ፆታዊ ጥቃቶች ተገቢው ትኩረት ይሰጣቸው!
በነውጥ አዘል ግጭቶች ወቅት እና አለመረጋጋት ባለባቸው ሁኔታዎች ሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶች መጠናቸው የሚጨምር ሲሆን፥ በአገራችንም ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል። ይሁንና የችግሩን አሳሳቢነት የሚመጥን ትኩረት አልተሰጠውም። ስለሆነም ጥቃቶቹን ለመከላከል፣ ለተጎጂዎችም የጤና እና ሥነ ልቦና ድጋፍ ለመስጠት፣ የጥቃቶቹን ፈፃሚዎች እና ተባባሪዎች ለሕግ ተጠያቂነት ለማቅረብ የፖሊሲ አቅጣጫዎች እንዲቀመጡ እና በቂ እርምጃዎች እንዲወሰዱ፣ ጉዳዩ በተለይ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፤
4ኛ) የተጋላጭ እና ግፉአን ጥበቃ ማዕቀፍ ይዘርጋ!
ነውጥ አዘል ግጭቶች በተከሰቱ ቁጥር የከፋ ሰቆቃ እና ጥቃት የሚደርስባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ኅዳጣን (minorities)፣ እንዲሁም ለጥቃት እና መድልዖ ተጋላጭ (vulnerable) ቡድኖች፤ በተለይም ሴቶች፣ ሕጻናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋዊያን እና ግፉዓን (marginalized) የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው። ለነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተገቢውን እና ልዩ ጥበቃ ማድረግ የሚያስችሉ አገራዊ፣ ሕጋዊ እና ተቋማዊ ማዕቀፍ እና አሠራሮች እንዲዘረጉ፤
5ኛ) ሕዝባዊ ተሳትፎ ይረጋገጥ!
በርካታ ግጭቶች እየተቀሰቀሱ ያሉት በፌዴራሉ እና ክልሎች መንግሥታዊ መስተዳድሮች የሚወሰኑ ውሳኔዎች የዜጎችን ትርጉም ያለው ተሳትፎ (meaningful participation) ያላረጋገጡ እና የብዙኃንን ይሁንታ ያላገኙ በመሆናቸው ነው ብለን እናምናለን። ስለሆነም፣ ሁሉም የመንግሥት አካላት መዋቅራዊ ለውጦችን በማድረግ፣ ማኅበረሰቦች ዘንድ ቅሬታ እና ጥርጣሬ ሊፈጥሩ የሚችሉ እርምጃዎችን ከመውሰዳቸው በፊትና ውሳኔዎችንም ከመወሰናቸው በፊት፣ ምክረ ሐሳቦቻቸውን ከባለድርሻ አካላት ጋር በግልጽ በመወያየት እና በሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ የብዙኃንን ይሁንታ በቅድሚያ እንዲያገኙ፤
6ኛ) የቅድመ ግጭት መጠቆሚያ እና መከላከያ ስርዓት (early warning system) ይኑር!
ቅሬታዎች ወደ ነውጥ የሚሸጋገሩበት ሒደት በተደጋጋሚ ቀድሞ የሚስተዋል መሆኑን እስካሁን ኢትዮጵያ ከገጠሟት ጦርነቶች እና ነውጥ አዘል ግጭቶች ትምህርት መውሰድ ይቻላል። ስለሆነም፣ ወደ ነውጥ አዘል ግጭቶች ሊሸጋገሩ የሚችሉ ውጥረቶችን ቀድሞ በመገምገም ግጭት መጠቆሚያ (alerting) እና መከላከያ ሥራዎች የሚከናወኑበት ስርዓት በመዘርጋት መንግሥት ግዴታውን እንዲወጣ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት እና ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶችም በግጭቶች እየደረሱ ያሉ ተጨማሪ ጉዳቶችን ለመከላከል በቂ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ፤
7ኛ) የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ሳይስተጓጎል ይቀጥል!
በጦርነትና በተለያዩ ክልሎች በተከስቱ ግጭቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ፣ ቤትና ንብረታቸው የወደመባቸው፣ በዚሁም ምክንያት በተፈናቃዮች የመጠለያ ካምፖች የሚገኙ እና ለርሃብና እርዛት የተጋለጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች አፋጣኝ፣ የማይስተጓጎል እና በቂ የሆነ የምግብ፣ የጤና አገልግሎት እና ሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች፣ በዘለቄታውም የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ በማናቸውም ሁኔታ ሳይገደቡ እና ሳይቆራረጡ በሚመለከታቸው አካላት ሊቀርቡላቸው ይገባል። ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ድርጅቶች በድጋፍ አሰጣጥ ሒደት ላይ የሚገጥሟቸውን አስተዳደራዊም ሆነ ሌሎች መሰናክሎች ምክንያት በማድረግ በአስከፊ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ የጥቃት ጉዳተኞች ድጋፍ ጠባቂዎች የሚያቀርቧቸውን ድጋፎች ሳያስተጓጉሉ እንዲቀጥሉ፤ በሒደቱ ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መንግሥት ተገቢውን አስተማማኝ የተጠያቂነት ስርዓት እንዲዘረጋ፤
8ኛ) የጥላቻ ንግግር እና የተዛቡ መረጃዎች ስርጭት ይቁም!
የጥላቻ ንግግሮች እና ግጭት ቆስቋሽ መልዕክቶች ነውጥ አዘል ግጭቶችን የሚያዋልዱ እና የሚያፋፍሙ መሆናቸውን ባለፉት ዓመታት አስተውለናል። የፖለቲካ ልኂቃን፣ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አቀንቃኞች እና ሌሎችም የተዛቡ መረጃዎችን ከማሰራጨት፣ ብሎም ሕዝብን በጅምላ ከሚፈርጁ ወይም ግጭቶችን ከሚቆሰቁሱ እና ከሚያባብሱ የቋንቋ አጠቃቀሞች እና መልዕክቶች ራሳቸውን እንዲቆጥቡ፤
9ኛ) የሲቪክ ምኅዳሩ ጥበቃ ይደረግለት!
የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች እና ጋዜጠኞች፣ እንዲሁም የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ሚዲያዎች በሥራዎቻቸው ሳቢያ የዘፈቀደ እስር፣ ማሰቃየት፣ አስገድዶ መሰወር፣ ሞት እና ሌሎችም የማዋከብ ድርጊቶች እየተፈፃሙባቸው ይገኛል። ይህም በሕግ የተሰጣቸውን ሐሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ እና የመሰብሰብ መብቶቻቸውን የሚያፍን እና የሥራ ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ የሚያደናቅፍ በመሆኑ የሚዲያ እና ሲቪክ ምኅዳር በቂ ጥበቃ እንዲደረግለት መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ፤
10ኛ) ባለድርሻ አካላት ለሰላም ግንባታ የበኩላቸውን ይወጡ!
ሰላም የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብር የሚፈልግ በመሆኑ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ እምነት ተኮር እና ማኅበረሰብ ዐቀፍ ተቋማት እንዲሁም ባሕላዊ ተቋማት በቅንጅት እና በተናጠል የሚጠበቅባቸውን በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
እኛም የዚህ የሰላም ጥሪ አቅራቢዎች የታመቁ ቅራኔዎች ወደ ነውጥ እንዳይሸጋገሩ ለመከላከል፣ ነውጥ አዘል ግጭቶች በሰላማዊ ንግግሮች እንዲፈቱ፣ እንዲሁም የሰላም ጅምሮች ሁሉን አካታች እና ዘላቂ እንዲሆኑ የድርሻችንን አስተዋፅዖ ለማበርከት፤ እንዲሁም ከላይ ባቀረብናቸው ጥሪዎች መሳካት ላይ አስፈላጊ የሆኑ ተግባራዊ ሥራዎችን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆናችንን ለመግለጽ እንወዳለን።
አዲሱ የ2016 ዓመት ለችግሮቻችን ሁሉ ሰላማዊ እና ዘላቂ መፍትሔ የምናበጅበት፣ ግጭቶች የተወገዱበት፣ ሰብዓዊ መብቶች በአግባቡ የሚከበሩበት፣ ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች ሙሉ ጥበቃ የሚያገኙበት፣ የጥላቻ ንግግሮች የሚቆሙበት፣ የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥበት፣ ለሰላም ግንባታ እና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን የዜጎች ንቁ ተሳትፎ የሚታይበት እንዲሆን መልካም ምኞታችንን እናቀርባለን።
መልካም አዲስ ዓመት!
የዚህ የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ አቅራቢ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚከተሉት ነን፤
- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት (CEHRO)
- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (EHRCO)
- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC)
- የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD)
- ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (AHRE)
- የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (EWLA)
- የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች (LHR)
- ሴታዊት ንቅናቄ
- ኢንተርአፍሪካ ግሩፕ (IAG)
- የኢትዮጵያ ሴቶች መብቶች ተሟጋች (EWRA)
- የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (NEWA)
- የኢትዮጵያ ሰራተኞች መብት ተሟጋች (ELRW)
- ሁሉን ዐቀፍ ራዕይ ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ (IVIDE)
- ኢስት አፍሪካን ኢኒሼቲቭ ፎር ቼንጅ (I4C)
- የሴቶች ህብረት ለሰላምና ለማህበረሰብ ፍትህ (WAPSJ)
- ልማት ለሁሉም (DFA)
- አዲስ ፓወርሃውስ (APH)
- ኢትዮጵያዊ ተነሳሽነት ለሰብዓዊ መብቶች (EIHR)
- ጉድ ሳማሪታን ማህበር (GSA)
- ሲቄ ዉሜንስ ዴቨሎፕመንት አሶስዬሽን (SWDA)
- ሴቶች ይችላሉ ማኅበር (WCDI)
- ሙጀጀጓ ሎካ የሴቶች ልማት ማኅበር (MLWD)
- ሳራ ፍትሕ ከሁሉም የሴቶች ማኅበር
- የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር (EWDNA)
- ኢንሃንስድ ቻይልድ ፎከስድ አክቲቪቲስ (ECFA)
- ሚዛን ወጣት የሕግ ባለሙያዎች ማዕከል
- ሰላም ለኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት
- መልካም እጆች ለሰላም፣ ዲሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት ግንባታ
- የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር
- ሚዛን የጋዜጠኞች ሞያ ምሩቃን ማኅበር
- መልካም አስተዳደር ለአፍሪካ-ምሥራቃዊ አፍሪካ (GGA-EA)
- የሰብአዊ መብቶች እና ሰላም ግንባታ ማዕከል (CPHRPB)
- ተስፋ ለሕፃናት ማኅበር (HFCA)
- ድሬ የተናጀ የማኅበረሰብ ልማት ድርጅት
- ሆፕፉል ጄኔሬሽን ፎር ዴቨሎፕመንት
For English Version New Year Peace Call-Joint call (English) 2016