Press statement

በኪነ-ጥበብ ስራዎች እና ባለሙያዎች ላይ የሚደረጉ ጫናዎች እንዲቆሙ  

ለመንግስት የቀረበ ጥሪ  

“ኪነ-ጥበብን ማፈን የሃሳብ ነፃነትን መጋፋት ስለሆነ ተገቢ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል” ያሬድ ሃይለማሪያም (በኢትዮጰያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር)

ኪነ-ጥበብ የአንድ አገር የሥልጣኔ ደረጃ መገለጫ ከሆኑት ነገሮች አንዱና ዋነኛው ሲሆን  የአገሪቱ ጠቃሚ እሴቶች እንዲጎለብቱ፣ ጎጅ የሆኑት ደግሞ እንዲታረሙ ለማድረግ፣ ማህበረሰብን ለማስተማሪያነት እና የሕዝብ ልብ ትርታም የሚገለጽበት የማህበረሰብ እሴት ነው፡፡ ኪነ-ጥበብ ለሰብአዊ መብቶች ግንዛቤ መዳበር፣ መጎልበት እንድሁም  መስፋፋት እና መከበር ያለው ጉልህ ሚና እጅግ የላቀ ነው፡፡ በተለይም የኪነ-ጥበብ መድረኮች እና ባለሞያዎች በሙዚቃ፣ በቲያትር፣ በግጥም፣ በስዕል እና በቅርፃቅርፅ መልክ የሚያንጸባርቋቸው ሃሳቦች የዜጎች ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት መገለጫዎች ናቸው። እነዚህ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች ለአንድ ማህበረሰብ የደስታም ሆነ የብሶት ሃሳቦቹን የሚገልጽባቸው መንገዶች የመሆናቸውን ያህል በአገር አስተዳደር ኃላፊነት ላይ ለተቀመጡ ወይም ለመንግስት አካላት ደግሞ የሕዝብን ጥያቄዎች፣ ስጋቶች፣ እርካታዎች ወይም ብሶቶችን በማድረስም ረገድ ልክ እንደ ሌሎች መገናኛ ብዙሃን የሚጫወቱት ሚና እጅግ ከፍ ያለ ነው።  

ኪነ-ጥበብ ከመዝናኛነት ያለፈ ማህበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖረው ሙሉ የሆነ ነጻነትን ይሻል። የሕግ ጥበቃም ይፈልጋል። ኪነ-ጥበብ ማህበረሰብን በሚያንጽና አገርን በሚጠቅም መልኩ የሚኖረውን አወንታዊ ሚና እንዲጫወት  በሃገራችንም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ የሕግ ጥበቃ ተደርጎለታል። በተለይም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 29 ላይ በግልጽ እንደተደነገገው ጥበብ እንደ አንድ ሃሳብን በነፃነት የመግለጫ መንገድ የህግ ከለላና እውቅና አግኝቷል::  

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወድህ በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እና የጥበብ ሥራዎች ወይም የኪነ-ጥበብ መድረኮች ላይ እየደረሱ ያሉ ወከባዎች፣ ክልከላዎች፣ እስሮችና ጫናዎች ከዕለት ዕለት እየበረቱ መምጣታቸው ድርጅታችንን ያሳስበዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ በጥር ወር 2016 ዓ.ም ወቅታዊ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማህበረዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት ተከታታይ “ቧለቲካ” የቴአትር መድረክ መከልከሉ የሚታወስ ነው፡፡ በተመሳሳይ በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም ማህበራዊ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት “እብደት በህብረት” የተሰኘው የመድረክ ተውኔት አዘጋጅና ተዋናይ ባለሙያዎች መታሰራቸውን ድርጅታችን አረጋግጧል። በተመሳሳይ ሁኔታም የተለያዩ እንደ ስነ-ፅሁፍ፣ ተውኔት እና የመሳሰሉት ስራዎች የሚቀርቡባቸው የጥበብ መድረኮች የስብሰባ ፍቃድ ያስፈልጋችኋል በሚል መስተጓጎጎላቸውን ተረድተናል፡፡ 

ድርጅታችን ኪነ-ጥበብ የሕዝብ ሃብት ከመሆኑም ባሻገር ለሰብአዊ መብቶች መከበርና በተለይም ሃሳብን በነጻነት ለማሰራጨት የሚጫወተውን ጉልህ ሚና ከግምት በማስገባት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚከታተላቸው የሰብአዊ መብት ዘርፎች አንዱ ነው። ስለሆነም በጥበብ ላይ የሚደረጉ ጫናዎች ማህበረሰቡ ሃሳቡን በነፃነት እንዳይገልፅ የሚያደርጉ፣ ህገ-መንግስታዊ መብትን ወይም ነፃነትን የሚጋፉ መሆናቸውን ያምናል፡፡ ድርጅታችን አንዳንድ የጥበብ አገላለጾች የሰላ ትችት ቢሆኑም እንኳን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ነጻነት ውስጥ የሚወድቁ መሆናቸውን ለማስገንዘብም ይወዳል። ሕገ-መንግስቱም ተገቢው ጥበቃ ይደረግላቸው ዘንድ በግልጽ ይደነግጋል።  

ይህን መነሻ በማድረግም ድርጅታችን የሚከተሉትን ምክረ ሃሳቦች ለመንግስት እና ለሚመለከታቸው አካላት ያቀርባል፡- 

  • መንግስት በህገ-መንግስቱ እና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች ላይ ጥበቃ የተደረገለትን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንድያከብር እና በዘፈቀደ እንዳይጣስም ጥበቃ እንድያደርግ፤ 
  • መንግስት ጥበብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና እና ፖለቲካዊ እድገት ያለውን ፋይዳ ከግንዛቤ በማስገባት ለጥበብ ባለሙያዎች እና ስራዎቻቸውቹ ሁኔታ መፍጠር እና ሃሳባቸውን እንድያቀርቡ ምህዳሩን  በማስፋት ድርሻውን እንዲወጣ፤ እንዲሁም 
  • በሥራቸው ምክንያት የታሰሩ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ከእስር እንዲፈቱ ወይም የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኙና የተከለከሉ የኪነ-ጥበብ መድረኮችም በነጻነት እንዲሰሩ፤ 

               አበክረን እንጠይቃለን፡፡                                    

ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም 

Related posts