ግፍን እንጠየፋለን፤ በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የጅምላ ግድያዎች ይቁሙ!
(JULY 1,2022)
እኛ የሴት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጥምረት አባላት እንዲሁም ከታች ስማችን የተዘረዘረው የሲቪክ ማህበራት ድርጂቶች አገራችን ሰላም የሰፈነባት፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የተገነባባት፣ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት እና ማህበራዊ ፍትሕ የጸናባት አገር እንድትሆን ካለን ጽኑ እምነት በመነጨ ትኩረታችንን ሰብአዊ መብቶች ላይ በማድረግ የበኩላችንን ድርሻ እያበረከትን እንገኛለን። የዛሬ አራት አመት በአገራችን የተከሰተው የፖለቲካ ለውጥ እና ይዟቸው በመጡም መልካም ዕድሎች በመጠቀም በተለያየ ዘረፍ ተሰማርተን እየሰራን እና በጋራም ተደራጅተን ለራሳችን መብት እና ለዜጎች መብት እና ነጻነት መከበር እየሰራን እንገኛለን። ይሁንና ይህ ተስፋችንን የሚያጨልሙ መጥፎ ተግባራትን በአፋጣኝ እንዲታረሙ እና እንዲስተካከሉ ድምጻችንን በጋራ በመሆን ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ እናሰማለን።
በአገራችን ላይ ተስፋ እንድናደርግ የሚያደርጉን በርካታ ነገሮችን ብናይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተደጋገሙ የሚከሰቱን የጅምላ ግድያ፣ የሕጻናት ሴቶች፣ የልጃገረዶች እና የሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ መደፈር እና ለወሲባዊ ጥቃቶች መጋለጥ፣ የሚሊዮኖች መፈናቀል፣ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ሰላም መታጣት፣ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ በማንነት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች እና በሰሜን የተጀመረው ጦርነት ሙሉ በሙሉ ገና እልባት ያላገኘ መሆኑ እኛን ለሰብአዊ መብቶች መከበር የምንታገል ኢትዮጵያዊያን ሴቶች እንዲሁም ሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች እጅግ ከማሳሰብም ባለፈ እንቅልፍ ነስቶናል። በታጣቂ ኃይሎች በየጊዜው በተለያዩ ክልሎች የሚፈጸሙት የጅምላ ግድያዎች በጊዜ አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት አለመቻላቸው የጥቃቱ መጠን እና የጭካኔ ደረጃዎች እያደገ እንዲሄድ አድርጓል የሚል እምነት አለን።
በተለይም በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደጋጋሚ፤ እንዲሁም በአማራ እና በአፋር ክልል ውስጥ አልፎ አልፎ እየተፈጸሙ ያሉት በንጹሐን ዜጎች ላይ ያነጣጠሩት ጥቃቶች ዋነኛ ሰለባዎች የሆኑት ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸው ሃዘናችንን ድርብ ያደርገዋል። እንዲሁም ጦርነቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል ውስጥ ንጹሐን ዜጎች የጥቃት ኢላማ መሆን፣ በሕክምና እጥረት እና በቂ የሆነ የሰብአዊ እርዳታ አለመኖር የዜጎች ህይወት እንዲሁ ለከፋ አደጋ መዳረጉ እንደ ኢትዮጵያዊ የሴት መብት ተሟጋቾች ሁኔታው እጅግ ያሳስበናል።
እነዚህን መሰል በንጹሐን ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ሆነ አጥፊዎችን ለፍርድ ለማቅረቡ ሰፊውና ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ በመቆም እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎችን በቃ! ሊላቸው ይገባል። መንግስትም በመላ አገሪቱ ሰላም የማስከበር፣ የዜጎችን ሕይወት ከማናቸውም ጥቃት የመከላከል፣ በመንግስት ውስጥ ያሉትንም ሆነ በኢ-መደበኛ አደረጃጀት ታጥቀው ሕዝብ ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ አካላትን ወደ ፍርድ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ ለማሳሰብ እንወዳለን።
በግፍ የተገደሉ ወገኖቻችንን ነፍስ ይማር!
ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን እንመኛለን!